Sunday, December 23, 2018

ትዕግስት

አንድ ካህን አባት አንድ ትዕግስት የጎደለው ወጣት የንስሀ ልጅ ነበራቸው ።ይህ ወጣት በትንሹም በትልቁም ቱግ እያለ፤ሰዎችን ያስቀይም ነበር።ከአንደበቱ ክፉ ቃላቶችን ስለሚያወጣ ከሰው ጋር መስማማት አልቻለም።ትዕግስት ፈፅሞ የለውም።ይህ ነገር እጅግ ያሳሰባቸው አባትም፤ልጁን የሚለውጡበት ዘዴ ሲያወጡ ሲያወርዱ ቆይተው አንድ መፍትሄ ላይ ደረሱ።አንድ ቀንም በቀረጢት ሙሉ ሚስማር ያዙና ልጁን አስጠርተው እንዲህ አሉት“ልጄ ሆይ …ይህን በቀረጢት ያለውን ሚስማር ተቀበለኝ፤ሁሌም ትዕግስት በጎደለህ ጊዜ እና ሰው ባስቀየምክ ቁጥር አንድ ሚስማር የእንጨቱ አጥር ላይ ሰካ” አሉት።ልጁ ምንም ግራ ቢገባውም አባቱ እንዳዘዙት ማድረግ ጀመረ።በመጀመሪያ ሰሞን በጣም ብዙ ሚስማሮችን ሰካ….ቀስ እያለ ግን በቀን እንጨቱ ላይ የሚሰካቸው ሚስማሮች ቁጥር እየቀነሰ መጣ…. እያለ…እያለ….በመጨረሻ ምንም ክፉ ያልተናገረ ቀን አንድም ሚስማር ሳይሰካ ዋለ።ልጁ በጣም ታጋሽ ሆኖ ባህሪው ተስተካከለ ማለት ነው።ይህንንም ለአባቱ አበሰረ።
አባም “ እሰይ ልጄ……አሁን ደግሞ ምንም ያልተናደድክ ቀን እና ክፉ ያልወጣህ ቀን በፊት ከሰካሃቸው ሚስማሮች ውስጥ አንዱን ንቀል” አሉት።ልጁ እንደተባለው አደረገ፤ከቀናት በኋላ ሁሉንም ሚስማሮች ነቅሎ ጨረሰ።ወደ አባም ሄዶ ሚስማሮችን አስረከበ።አባም አንዲህ አሉት
“አየህ ልጄ……አሁን የሰካሃቸውን ሚስማሮች ነቅለህ ጨርሰሃል…..በጣም ታጋሽ ሆነሃል ማለት ነው፤ነገር ግን እስቲ አጥሩን ተመለክት….ፈጽሞ እንደ ድሮው ሊሆን አይችልም፤ሚስማሩ ቢወጣም ተበሳስቷል።ክፉ ንግግርም ልክ እንደ ሚስማር ነው፤ሺህ ጊዜ ይቅር ብትልም፤እንደሚስማሩ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል ፤እናም ልጄ……..በህይወት ትዕግስት ይኑርህ…..አንደበትህን ቆጥብ” ብለው አስተማሩት።.አንደበት ይገራል፤አንደበትን የሚገራው መልካም አስተሳሰብ ነው።በክፉ ንግግር ፤በጭቅጭቅ፤በስድብ እስከዛሬ ምን መልካም ነገሮች ሲፈጠሩ አየን? ስህተቶቻችን እየጎለጎልን በመነካከስ ምን ልዩነቶችን አጠበብን?………”ቃላት” ለሰው ልጅ ኑሮ የእስትንፋስ ያህል ዋጋ አለው።በቃላት ጦርነት ይነሳል፤በቃላት ሰላም ይሰፍናል…….
እስቲ ለጥቂት ቀናት እራሳችንን እንፈትነው…….መልካም መልካሙን በመናገር
©ዲ/ን ጌታመሳይ ኃይለሚካኤል

Friday, December 21, 2018


አዶልፍ ሂትለር (ጀርመንኛ : Adolf Hitler አዶልፍ ሂትለ) እ.አ.አ. ከ1933 ጀምሮ የ ጀርመን ቻንስለር እንዲሁም ከ1934 ጀምሮ ደግሞ የጀርመን መሪም
(Führer) ጭምር የነበረ ሰው ነው።

አዶልፍ ሂትለር
Adolf 
የተወለዱበት ቀን
ሚያዝያ 13 1881
ያረፉበት ቀን
ሚያዝያ 22 1937
ፓርቲ
ብሔራዊ ሶሻሊስት ጀርመን ሰራተኞች ፓርቲ
ዋና ማዕረጎች
የብሔራዊ ሶሻሊስት ጀርመን ሰራተኞች ፓርቲ መሪ
የጀርመን ቻንስለር
ሕይወት

ሂትለር በ ሚያዝያ 13 ቀን 1881 ዓ.ም. (20 አፕሪይል 1889 እ.ኤ.አ.) በዛሬይቷ ኦስትሪያ ተወለደ። በ ሚያዝያ 22 ቀን 1937 ዓ.ም. (30 አፕሪይል 1945 እ.ኤ.አ.) በርሊን ውስጥ ከአንድ ቀን በፊት ካገባት ሚስቱ ኤቫ ብራውን ጋር የራሱን ህይወት አጠፋ።
በ 1925 ዓ.ም. መጀመርያ የሂትለር ናዚ ወገን ከጓደኞቹ ወገን ጋር በ ራይክስታግ ምክር ቤት ትብብር መንግሥት ለመሥራት በቂ መንበሮች አልነበራቸውም። ተቃራኒዎቻቸው የ ኰሙኒስት ወገን 17% መንበሮች ስለ ነበራቸው የሂትለር ወገኖች የድምጽ ብዛት ሊያገኙ አልተቻላቸውም ነበር። በዚያው ዓመት ግን ከምርጫው ትንሽ በፊት የራይክስታግ ሕንጻ በእሳት ተቃጠለ። ይህ የኰሙኒስቶች ሥራ ነው ብለው የሂትለር ወገን ኰሙኒስት ፓርቲ ቶሎ እንዲከለከል አደረጉ። ስለዚህ ከምርጫው በኋላ የኰሙኒስትን መንበሮች ስለ አጡ የሂትለርም ወገኖች አሁን ከ50% መንበሮች በላይ ስላገኙ፣ የትብብር መንግሥት ሠሩና ወዲያው በድንጋጌ አቶ ሂትለር ባለሙሉ ሥልጣን አደረጉት።
ሂትለር የጻፈው የርዮተ አለሙ ጽሑፍ «የኔ ትግል» ( Mein Kampf) ሟርት ብቻ ነው። ለመጥቀስ ያህል፦ «ትኩረቴ ወደ አይሁዶች ስለ ተሳበ፣ ቪየና ን ከበፊት በሌላ ብርሃን ለማየት ጀመርኩ። በሄድኩበት ሁሉ አይሁዶችን አየሁዋቸው፤ በብዛትም እያየኋቸው፣ ከሌሎች ሰዎች ፈጽሞ እንድለያቸው ጀመርኩ።»... «የግዛቱ (ኦስትሪያ-ሀንጋሪ ) ዋና ከተማ የከሠተውን የዘሮች ውሑድ ጠላሁት፤ የዚህን ሁሉ የቼኮች፣ ፖሎች፣ ሀንጋርዮች፣ ሩጤኖች፣ ሰርቦች፣ ክሮዋቶች ወዘተ. የዘሮች ድብልቀት፤ በሁላቸውም መካከል፣ እንደ ሰው ልጅ መከፋፈል ሻገቶ፣ አይሁዶችና ተጨማሪ አይሁዶች።»
ፖለቲካ

በነበረው ዘረኛ አስተዳደሩ 6 ሚሊዮን የ አውሮፓ
አይሁዶችን እና የተለያዩ ሀገራት ህዝቦችን በገፍ አስጨርሷል።
በሂትለር ሥር የናዚዎች ፍልስፍና በ ሂንዱኢዝም እንደሚገኘው በዘር የተከፋፈለ ካስት ሲስተም መመሥረት አይነተኛ ነበር። « አርያኖች» የተባሉት ዘሮች በተለይም የ ጀርመናውያን ብሔሮች ከሁሉ ላዕላይነት እንዲገኙ አሠቡ። ይህ ዝብረት የተነሣ በ ርግ ቬዳ ዘንድ በ1500 ዓክልበ. ያህል ወደ ሕንድ የወረሩት ነገዶች «አርያን» ስለ ተባሉ ነው፤ በጥንትም «አሪያና » የ አፍጋኒስታን አካባቢ ስም የዘመናዊው
ኢራን ም ሞክሼ ነበር። በናዚዎቹ እንደ ተዛበው ግን ታሪካዊ ባይሆንም የ«አርያኖች» ትርጓሜ ጀርመናውያን ብቻ ነበሩ፤ ስላቮች (በተለይ የሩስያ ና የፖሎኝ ሕዝቦች) ግን አርያኖች ሳይሆኑ እንደ ዝቅተኞች ተቆጠሩ። የሂትለር እብደት እየተራመደ በ1926 ዓም የ ሀንጋሪ ሕዝብ ደግሞ «አርያኖች» ተደረጉ፣ በ1928 ዓም የ ጃፓን ሕዝብ እንኳን በይፋ «አርያኖች» ተደረጉ፤ በ1934 ዓም የ ፊንላንድ ሕዝብ ወደ «አርያኖች» በሂትለር ዐዋጅ ተጨመሩ። በ ሙሶሊኒ ሥር የ ፋሺስት ጣልያኖች እኛም አርያኖች ነን ቢሉም ጣልያኖች አርያን መሆናቸው በናዚዎች ዘንድ መቸም አልተቀበለም ነበር።


Tuesday, December 18, 2018


{`ከአሜን ባሻገር`}
======
"በዘመናችን #ብሔርተኝነት ማለት ሳይደክሙ የሌሎችን የድካም ውጤት መቀማት መሆኑን አውቃለሁ። አንድ ሰው በግሉ ስኬት መቀዳጀት ሲያቅተው በጥረታቸው ብልጫ ያስመዘገቡ ግለሰቦችን ስኬት ወደ ብሄር ስኬት ለውጦ ባዶነቱን ለመሙላት ይሞክራል። ሌላው÷እልም ያለ ፈሪ ሆኖ ሳለ "የበላይ ዘር" እያለ ይፎክራል። ብብቱ ውስጥ ገብተው ካልደገፉት በቀር አልጋ ላይ መውጣት የማይችለው ሰውዬ÷ አበበ ቢቂላ በተነሳ ቁጥር "አበበ ኬኛ" እያለ ይኩራራል። በላይና አበበ ያስመዘገቡት ድል በላብና በደም የተገኘ የግለሰብ ጥረት ውጤት ነው። ድል በዘር አይተላለፍም። የአባቶች ታላቅነት በዘር ወደ ልጆች የሚተላለፍ ቢሆን ኖሮ ግሪኮች በዛሬይቱ የአውሮፓ እግር ስር እንደጉድፍ ወድቀው ባልተገኙ ነበር። ብሔርተኝነት የግለሰብ ጥረትን ሰርቆ የራስን ድክመት ለመሙላት የሚደረግ መሰሪ እንቅስቃሴ ነው።"
.
©በዕውቀቱ ስዩም
{ከአሜን ባሻገር}

ምርጥ ሃያ የማርከስ ቱሊስ ሲስሮ አባባሎች!

ወዳጆች ዛሬ አባባሎቹን የምንዘክርለት ታላቅ ሠው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመስከረም 106 ዓ.ዓ. እስከ ታህሳስ 43 ዓ.ዓ. ድረስ የኖረው ሮማዊው ፈላስፋ፣ ፖለቲከኛ፣ የአደባባይ ተናጋሪና የሕግ ሊቅ የነበረውን ሲስሮን ነው፡፡ ሲስሮ በሙሉ ስሙ ማርከስ ቱሊስ ሲስሮ (Marcus Tullius Cicero) በመባል ይታወቃል፡፡
ይሄ ሠው በሮማ ታሪክ አንደበተ ርቱዕና ታላቅ የስነፅሁፍ ሠው ተደርጎም ይቆጠራል፡፡ በውብ የአጻፃፍ ስልቱ ለላቲን ቋንቋ ማደግ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት የሲስሮ አስተዋፅኦ በላቲን ቋንቋ ብቻ ሳይወሰን በአብዛኛው የአውሮፓውያን ቋንቋና የስነፅሁፍ ዕድገት ላይም ተፅዕኖውን እንዳሳረፈ ይጠቅሳሉ፡፡ ሲስሮ የግሪክ ፍልስፍናን ለሮማውያን ያስተዋወቀና በላቲን መዝገበ ቃላት ውስጥ የፍልስፍና ቃላትን የፈጠረ ሠው ነበር፡፡
ጆን አዳምስ የተባለ ፀሐፊ ሲስሮን ሲገልጸው እንዲህ ይላል፡- ‹‹እስካሁን ባየነው የዓለማችን እድሜ ዓለም ፖለቲካንና ፍልስፍናን አቆራኝቶ የያዘን ታላቅ ሠው ፈጥራ አታውቅም (“All ages of the world have not produced a greater statesman and philosopher combined.”) በማለት ሲስሮ እነዚህን አቆራኝቶ የያዘ መሆኑን መስክሯል፡፡
አንቶኒ ኤቨሪት (Anthony Everitt) የተባለ ፀሐፊ “የታላቁ የሮማ ፖለቲከኛ ህይወትና የሕይወት ጊዜው” (Cicero: The Life and Times of Rome's Greatest Politician) በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሐፉ ውስጥ ስለሲስሮ ታላቅነት የመሠከሩ የታላላቅ የሶስት ሠዎችን ምስክርነት አስቀምጧል፡፡
አንደኛውም ቮልቴር ነው፡፡ ቮልቴር እንዲህ አለ፡- ‹‹ሲስሮ እንዴት ማሠብ እንዳለብን አስተምሮናል (“He taught us how to think.)" በማለት አድንቆታል፡፡
ሁለተኛው ኤድዋርድ ጊበን የተባለም ሠው ሲሆን፤ እሱም እንዲህ ይላል፡- ‹‹የቋንቋውን ውበት አጣጥሜዋለሁ፣ የነፃነትን መንፈስ ተንፍሼበታለሁ፣ በግለሰብ ዘንድ ያለውን ስሜትም ይሁን በህዝቦች ዘንድ ያነሳቸውን ሃሳቦችና ምሣሌዎች ሁሉ ምጥጥ አድርጌአለሁ፡፡ (“I tasted the beauties of language, I breathed the spirit of freedom, and I imbibed from his precepts and examples the public and private sense of a man.”)›› በማለት አድናቆቱን ገልፅዋል፡፡
ሶስተኛውና ምስክርነት የሠጡት ታላቅ ሠው ኩባን ለብዙ ዓመታት የመሩት ፊደል ካስትሮ ናቸው፡፡ እኚህም ሠው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሲስሮ ማን ነበር፤ ሲስሮ አንደበተ ርቱዕና የልብ ተናጋሪ ሠው ነበር፡፡ (“Who was Cicero: a great speaker or a demagogue?” )›› በማለት የልብ ተናጋሪነቱን አሞግሠዋል፡፡
ወዳጆች ስለሲስሮ ይቺን ታህል ካልኩ ዘንዳ የተናገራቸውን አባባሎች ሃሳብ እንድገዛባቸውና ሌላ አዲስ ሃሳብ እንድንፈጥርባቸው እነሆ እላለሁ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ሃሳብን ያሳድጋልና ሃሳባችሁን ወዲህ በሉ፡፡
1. ‹‹ምስጋና ታላቅና መልካም ስነምግባር ብቻ ሳይሆን የበጎ ነገሮች ሁሉ ወላጅ ነው፡፡››
2. ‹‹ተፈጥሮ በአዕምሮአችን ውስጥ በቀላሉ የማይረካ እውነትን የሚናፍቅ ተክል ተክላለች፡፡››
3. ‹‹ታሪክ የዘመን ምስክር፣ የእውነት ብርሃን፣ የኑሮ ማስታወሻ፣ የሕይወት አስተማሪ፣ እንዲሁም የጥንት ስራ መልዕክተኛ ነው፡፡››
4. ‹‹ታሪክን የምናጠናው በሌላ ጊዜ ጎበዝ ለመሆን ሳይሆን ሁልጊዜም ብልህ ለመሆን ነው፡፡››
5. ‹‹የፍትህ መሠረት ጥሩ እምነት ነው፡፡››
6. ‹‹ሕይወት ባለበት ሁሉ ተስፋ አለ፡፡››
7. ‹‹የሟች ሕይወት በሕያዋን አዕምሮ ውስጥ ይቀመጣል፡፡››
8. ‹‹በማሕበራዊም ይሁን በግል ሕይወት የሞራል ግዴታውን የሚያራቁት ምንም ነገር የለም፡፡››
9. ‹‹ከታሪክ ምንም አልተማርንም፡፡ የተማርነው ከታሪክ ምንም መማር አለመቻላችንን ነው፡፡››
10. ‹‹አዕምሮን መኮትኮት ሠውነትን በምግብ ከመገንባት እኩል አስፈላጊ ነው፡፡››
11. ‹‹አንድ ህግ አለ፡፡ ይሄ ህግ በወረቀት የተፃፈ ሳይሆን በልባችን ላይ በተፈጥሮ የተከተበ ነው፡፡ ህጉ በስልጠና ወይም በማንበብ ያገኘነው ሳይሆን ተፈጥሮን በመላመድ የተዋሃድነው ነው፡፡ ህጉ ወደእኛ የመጣው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር፣ በመመሪያ ሳይሆን በተፈጥሯዊ ስሜት እውን የሆነ ነው፡፡ ይሄንን ተፈጥሯዊ ህግ እመርጠዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ምንም አይነት አደጋ ሲጋረጥብን፣ ጠላት አልያም ሌባ ሊተናኮለን ሲመጣ፤ እሱን ለመከላከል የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ከውስጣችን የሚፈልቅ ልባዊ ስሜታችን በመሆኑ ልክ ነው፡፡››
12. ‹‹አንድ አንደበተ-ርቱዕ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ሶስት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ለአድማጮቹ መረጃ ማቀበል፣ ሁለተኛ በንግግሩ ታዳሚውን ማስደሰት እና ሶስተኛው ወኔአቸውን መቀስቀስ ነው፡፡››
13. ‹‹ተፈጥሯዊው ፍጥረት በሠው ጥበብ ከተፈጠረው ጥበባዊ ስራ የበለጠ ፍፁም ነው፡፡
14. ‹‹ለሚያፈቅር ሠው ምንም የሚስቸግረው ነገር የለም፡፡››
15. ‹‹ማንም ስህተት ሊሠራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያንኑ ስህተት ይዞ የሚቀጥለው ደደብ ብቻ ነው፡፡››
16. ‹‹የአትክልት ስፍራና ቤተመፃህፍት ቤት ካለህ የምትፈልገው ነገር ሁሉ አለህ ማለት ነው፡፡››
17. ‹‹የሁሉም ነገሮች መጀመሪያ ትንሽ ነገር ነው፡፡››
18. ‹‹መፅሐፍ የሌለው ቤት ማለት ነፍስ የሌለው ስጋ ማለት ነው፡፡››
19. ‹‹ሕግ ሲበዛ ፍትህ ያንሣል!››
20. ‹‹ሁለት ዓይነት የፍትህ መመሪያዎች አሉ፡፡ አንደኛው ማንም አለመጉዳት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለማሕበረሰቡ ደህንነት ዘብ መቆም ነው፡፡››
_________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሐሙስ ሠኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

Tuesday, December 4, 2018

ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል

ከታች የዘረዘርናቸውን መጽሀፍት ብታነቡልን

ጥሩ የአማርኛ መጽሀፍት (ጣመን ጣመን ድገሙን)
እነዚህን መጽሀፍት ያካተተ መደርደሪያ ምርጥ ነው።
ክፍል አንድ—ልብወለድ
1)አደፍርስ—ዳኛቸው ወርቁ
2)ፍቅር እስከ መቃብር—ሀዲስ አለማየሁ
3)ሀዲስ—በአሉ ግርማ
4)የታንጉት ሚስጥር—ብርሀኑ ዘርይሁን
5)ሌቱም አይነጋልኝ—ስብሃት ገብረእግዚአብሔር
6)ጉንጉን—ሀይለመለኮት መዋዕል
7)ግራጫ ቃጭሎች—አዳም ረታ
8)ከቡስካ በስተጀርባ—ፍቅረማርቆስ ደስታ
9)አንድ ለናቱ—አቤ ጉበኛ
ክፍል ሁለት—ግጥም
1)እሳት ወይ አበባ—ጸጋዬ ገብረ መድኅን
2)ልጅነት—ሰለሞን ደሬሳ
3)የግጥም ጉባኤ—መንግስቱ ለማ
4) ኗሪ አልባ ጎጆዎች—በእውቀቱ ስዩም
5)የቅኔ አዝመራ—ከበደ ሚካኤል
6)እንጉርጉሮ—መስፍን ወልደማርያም
7)አፈር ያነሳ ስጋ—ሰይፉ መታፈሪያ
8)ፍንዳታ—ኅይሉ ገብረ ዮሐንስ(ገሞራው)
9)መንገድ ስጡኝ ሰፊ—ገብረክርስቶስ ደስታ
10) እስቲ ተጠየቁ—ዮሐንስ አድማሱ
ክፍል ሶስት—ታሪክ
1)የኢትዮጵያ ታሪክ(ወደ ስምንት የሚጠጉ ሁሉም መጽሀፍት)—ተክለጻዲቅ መኩሪያ
2)የዕትዮጵያ ህዝብ ታሪክ—ታዬ ገብረማርያም
3)አጼ ቴዎድሮስ—አለቃ ዘነብ
4)የኢትዮጲያ ታሪክ በአስራስድስተኛው ክፍለ ዘመን—ይልማ ደሬሳ
5)የኤርትራ ጉዳይ—ዘውዴ ረታ
6)አጼ ምኒልክ—ጳውሎስ ኞኞ
7)የታሪክ ማስታወሻ—ደጃዝማች ከበደ ተሰማ
8)የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1868 እስከ 1966—ባህሩ ዘውዴ
9)Ancient and Medieval History of Ethiopia —ስርግው ሀብለስላሴ
10)Church and State in Ethiopia ታደሰ ታምራት
ክፍል አራት—ትርጉም
1)ነገም ሌላ ቀን ነው—ነብይ መኮንን
2)መከረኞቹ—ሳህለስላሴ ብርሀነማርያም
3)እፎይታ—ተሾመ ዳምጠው
4)ሀምሌት—ጸጋዬ ገብረመድኅን
5)ሮምዮና ዡልየት—ከበደ ሚካኤል
6)ታራስ ቡልባ —በካፋ ሀይለ እየሱስ
7)እናት—ግእዛን የማነ
8)ሲራኖ—ባሴ ሀብቴ
9)ወንጀልና ቅጣት—ካሳ ገብረህይወት እና ፋንቱ ሳህሌ
10)ሳቤላ—ኃይለስላሴ መሀሪ
11)ካፒታል