Tuesday, December 18, 2018

ምርጥ ሃያ የማርከስ ቱሊስ ሲስሮ አባባሎች!

ወዳጆች ዛሬ አባባሎቹን የምንዘክርለት ታላቅ ሠው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመስከረም 106 ዓ.ዓ. እስከ ታህሳስ 43 ዓ.ዓ. ድረስ የኖረው ሮማዊው ፈላስፋ፣ ፖለቲከኛ፣ የአደባባይ ተናጋሪና የሕግ ሊቅ የነበረውን ሲስሮን ነው፡፡ ሲስሮ በሙሉ ስሙ ማርከስ ቱሊስ ሲስሮ (Marcus Tullius Cicero) በመባል ይታወቃል፡፡
ይሄ ሠው በሮማ ታሪክ አንደበተ ርቱዕና ታላቅ የስነፅሁፍ ሠው ተደርጎም ይቆጠራል፡፡ በውብ የአጻፃፍ ስልቱ ለላቲን ቋንቋ ማደግ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት የሲስሮ አስተዋፅኦ በላቲን ቋንቋ ብቻ ሳይወሰን በአብዛኛው የአውሮፓውያን ቋንቋና የስነፅሁፍ ዕድገት ላይም ተፅዕኖውን እንዳሳረፈ ይጠቅሳሉ፡፡ ሲስሮ የግሪክ ፍልስፍናን ለሮማውያን ያስተዋወቀና በላቲን መዝገበ ቃላት ውስጥ የፍልስፍና ቃላትን የፈጠረ ሠው ነበር፡፡
ጆን አዳምስ የተባለ ፀሐፊ ሲስሮን ሲገልጸው እንዲህ ይላል፡- ‹‹እስካሁን ባየነው የዓለማችን እድሜ ዓለም ፖለቲካንና ፍልስፍናን አቆራኝቶ የያዘን ታላቅ ሠው ፈጥራ አታውቅም (“All ages of the world have not produced a greater statesman and philosopher combined.”) በማለት ሲስሮ እነዚህን አቆራኝቶ የያዘ መሆኑን መስክሯል፡፡
አንቶኒ ኤቨሪት (Anthony Everitt) የተባለ ፀሐፊ “የታላቁ የሮማ ፖለቲከኛ ህይወትና የሕይወት ጊዜው” (Cicero: The Life and Times of Rome's Greatest Politician) በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሐፉ ውስጥ ስለሲስሮ ታላቅነት የመሠከሩ የታላላቅ የሶስት ሠዎችን ምስክርነት አስቀምጧል፡፡
አንደኛውም ቮልቴር ነው፡፡ ቮልቴር እንዲህ አለ፡- ‹‹ሲስሮ እንዴት ማሠብ እንዳለብን አስተምሮናል (“He taught us how to think.)" በማለት አድንቆታል፡፡
ሁለተኛው ኤድዋርድ ጊበን የተባለም ሠው ሲሆን፤ እሱም እንዲህ ይላል፡- ‹‹የቋንቋውን ውበት አጣጥሜዋለሁ፣ የነፃነትን መንፈስ ተንፍሼበታለሁ፣ በግለሰብ ዘንድ ያለውን ስሜትም ይሁን በህዝቦች ዘንድ ያነሳቸውን ሃሳቦችና ምሣሌዎች ሁሉ ምጥጥ አድርጌአለሁ፡፡ (“I tasted the beauties of language, I breathed the spirit of freedom, and I imbibed from his precepts and examples the public and private sense of a man.”)›› በማለት አድናቆቱን ገልፅዋል፡፡
ሶስተኛውና ምስክርነት የሠጡት ታላቅ ሠው ኩባን ለብዙ ዓመታት የመሩት ፊደል ካስትሮ ናቸው፡፡ እኚህም ሠው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሲስሮ ማን ነበር፤ ሲስሮ አንደበተ ርቱዕና የልብ ተናጋሪ ሠው ነበር፡፡ (“Who was Cicero: a great speaker or a demagogue?” )›› በማለት የልብ ተናጋሪነቱን አሞግሠዋል፡፡
ወዳጆች ስለሲስሮ ይቺን ታህል ካልኩ ዘንዳ የተናገራቸውን አባባሎች ሃሳብ እንድገዛባቸውና ሌላ አዲስ ሃሳብ እንድንፈጥርባቸው እነሆ እላለሁ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ሃሳብን ያሳድጋልና ሃሳባችሁን ወዲህ በሉ፡፡
1. ‹‹ምስጋና ታላቅና መልካም ስነምግባር ብቻ ሳይሆን የበጎ ነገሮች ሁሉ ወላጅ ነው፡፡››
2. ‹‹ተፈጥሮ በአዕምሮአችን ውስጥ በቀላሉ የማይረካ እውነትን የሚናፍቅ ተክል ተክላለች፡፡››
3. ‹‹ታሪክ የዘመን ምስክር፣ የእውነት ብርሃን፣ የኑሮ ማስታወሻ፣ የሕይወት አስተማሪ፣ እንዲሁም የጥንት ስራ መልዕክተኛ ነው፡፡››
4. ‹‹ታሪክን የምናጠናው በሌላ ጊዜ ጎበዝ ለመሆን ሳይሆን ሁልጊዜም ብልህ ለመሆን ነው፡፡››
5. ‹‹የፍትህ መሠረት ጥሩ እምነት ነው፡፡››
6. ‹‹ሕይወት ባለበት ሁሉ ተስፋ አለ፡፡››
7. ‹‹የሟች ሕይወት በሕያዋን አዕምሮ ውስጥ ይቀመጣል፡፡››
8. ‹‹በማሕበራዊም ይሁን በግል ሕይወት የሞራል ግዴታውን የሚያራቁት ምንም ነገር የለም፡፡››
9. ‹‹ከታሪክ ምንም አልተማርንም፡፡ የተማርነው ከታሪክ ምንም መማር አለመቻላችንን ነው፡፡››
10. ‹‹አዕምሮን መኮትኮት ሠውነትን በምግብ ከመገንባት እኩል አስፈላጊ ነው፡፡››
11. ‹‹አንድ ህግ አለ፡፡ ይሄ ህግ በወረቀት የተፃፈ ሳይሆን በልባችን ላይ በተፈጥሮ የተከተበ ነው፡፡ ህጉ በስልጠና ወይም በማንበብ ያገኘነው ሳይሆን ተፈጥሮን በመላመድ የተዋሃድነው ነው፡፡ ህጉ ወደእኛ የመጣው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር፣ በመመሪያ ሳይሆን በተፈጥሯዊ ስሜት እውን የሆነ ነው፡፡ ይሄንን ተፈጥሯዊ ህግ እመርጠዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ምንም አይነት አደጋ ሲጋረጥብን፣ ጠላት አልያም ሌባ ሊተናኮለን ሲመጣ፤ እሱን ለመከላከል የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ከውስጣችን የሚፈልቅ ልባዊ ስሜታችን በመሆኑ ልክ ነው፡፡››
12. ‹‹አንድ አንደበተ-ርቱዕ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ሶስት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ለአድማጮቹ መረጃ ማቀበል፣ ሁለተኛ በንግግሩ ታዳሚውን ማስደሰት እና ሶስተኛው ወኔአቸውን መቀስቀስ ነው፡፡››
13. ‹‹ተፈጥሯዊው ፍጥረት በሠው ጥበብ ከተፈጠረው ጥበባዊ ስራ የበለጠ ፍፁም ነው፡፡
14. ‹‹ለሚያፈቅር ሠው ምንም የሚስቸግረው ነገር የለም፡፡››
15. ‹‹ማንም ስህተት ሊሠራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያንኑ ስህተት ይዞ የሚቀጥለው ደደብ ብቻ ነው፡፡››
16. ‹‹የአትክልት ስፍራና ቤተመፃህፍት ቤት ካለህ የምትፈልገው ነገር ሁሉ አለህ ማለት ነው፡፡››
17. ‹‹የሁሉም ነገሮች መጀመሪያ ትንሽ ነገር ነው፡፡››
18. ‹‹መፅሐፍ የሌለው ቤት ማለት ነፍስ የሌለው ስጋ ማለት ነው፡፡››
19. ‹‹ሕግ ሲበዛ ፍትህ ያንሣል!››
20. ‹‹ሁለት ዓይነት የፍትህ መመሪያዎች አሉ፡፡ አንደኛው ማንም አለመጉዳት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለማሕበረሰቡ ደህንነት ዘብ መቆም ነው፡፡››
_________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሐሙስ ሠኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

No comments:

Post a Comment